በትግራይ ክልል እርዳታ ማድረስ የተገደበ መሆኑን አለም አቀፉ ቀይ መስቀል አስታወቀ
ምንጭ፡ BBC
በጦርነት ክፉኛ ወደተጎዳችው ትግራይ ክልል ህይወት አድን የህክምና መገልገያዎችን ለማድረስ የሚደረገው ጥረት የተገደበ መሆኑን የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ አስታወቀ።
በባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲሁም የትግራይ ኃይሎች ሰብዓዊ የተኩስ አቁም ቢያደርጉም የእርዳታ አቅርቦቱ ላይ መሻሻሎች እንደሌሉ ተቋሙ ገልጿል።
ከአምስት ወራት እግድ በኋላ ከጥር ወር ጀምሮ የህክምና ቁሳቀሶችን በአውሮፕላን በረራዎች እንዲያስገባ የተፈቀደለት የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በየብስ እርዳታ ማስገባት እንዳልቻለ ለቢቢሲ አስረድቷል።
እርዳታ የጫኑ መኪኖቹ በመንገዱ “የጸጥታና መዳረሻ” ችግሮች ምክንያት ወደ ክልሉ መግባት እንዳልቻሉም ተጠቁሟል።
ቀይ መስቀል በባለፉት ሶስት ወራት በሰላሳ ስምንት በረራዎች አስፈላጊ የሆኑ መድኃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶችን ወደ ክልሉ ማድረስ ችሏል።
ነገር ግን በክልሉ ካለው መጠነ ሰፊ ፍላጎት ጋር ሲነፃፀር እየቀረበ ያለው “የውቅያኖስ ጠብታ ነው” ሲሉ በኢትዮጵያ የድርጅቱ ቃለአቀባይ ፋጢማ ሳቶር ተናግረዋል።
በክልሉ ባጋጠመው የመድኃኒትና የህክምና ቁሳቁሶች እጥረት ምክንያት በትግራይ የሚገኙ ዶክተሮች ጓንትን ጨምሮ ሌሎች ቁሳቁሶችን እንደገና እንዲጠቀሙ አስገድዷቸዋል ሲሉ ቃለ አቀባይዋ አስረድተዋል።
ቀይ መስቀል የእርዳታ ጭነት መኪኖቹ ወደ ክልሉ እንዲገቡ መፈቀዱ ተቐሙ የሚያደርገውን የእርዳታ አቅም በእጅጉ ያሳድጋል ብሏል።
የረድዔት ድርጅቶች የኢትዮጵያ መንግሥት ሆን ብሎ እርዳታን አግዷል ብለው የሚወነጅሉ ሲሆን መንግሥት ግን ይህንን አይቀበለውም።
በባለፈው ሳምንት የተኩስ አቁሙን ተከትሎም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እርዳታ ወደሚፈልጉበት ትግራይ ክልል አስፈላጊው እርዳታ ሊገባ ይችላል የሚል ተስፋን ፈንጥቋል።
ሆኖም የኢትዮጵያ መንግሥት እና የህወሓት ባለሥልጣናት የህክምና ቁሳቁሶችን ጨምሮ የእርዳታ አቅርቦትን በማደናቀፍ እርስ በእርሳቸው እየተወቃቀሱ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ሲባል ግጭት ማቆሙን ካሳወቀ በኋላ ከህወሓት በኩል አስፈላጊው ትብብር ባለመኖሩ በየብስ እርዳታ ትግራይ ማድረስ አልቻልኩም ብሏል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ክልል ላሉ ዜጎች በየብስ እርዳታው ለማቅረብ ጥረት ቢያደርግም ህወሓት ሊተባበር ባለመቻሉ የእርዳታ አቅርቦት ሥራው እክል ገጥሞታል ብሏል።
በተመሳሳይ ህወሓት ባወጣው መግለጫ ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑን አስታውሶ፤ ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ ወደ ትግራይ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እየቀረበ መሆኑን ያረጋግጥ ሲል ጥያቄ አቅርቧል።
ሆኖም በዛሬው ዕለት የዓለም ምግብ ፕሮግራም እርዳታ የጫኑ መኪኖቹ ኢሬፕቲ የምትባል ከተማ እንደደረሱና ወደ ትግራይ መዲና መቀለ በቅርቡ እንደሚገቡ ተቋሙ አስታውቋል።
ከ500 ሜትሪክ ቶን በላይ የምግብ እርዳታም በረሃብ አፋፍ ላይ ላለው ህዝብ ይደርሳል ብሏል የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትዊተር ገጹ።
ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል መሰረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶች መብራት፣ ውሃ፣ ስልክ፣ ትራንስፖርትና የባንክ አገልግሎቶች አሁንም እንደተቋረጡ ናቸው።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በሰሜን ኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልገው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጿል።
አስራ ሰባት ወራት ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረትና ሌሎች አጋሮች ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሃት ለሰብዓዊነት ሲባል የተኩስ አቁም ያወጁ ሲሆን ይህም ለሰላም በር ሊከፈትና ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማብቃት ወደሚያስችል ውይይት እንደሚችል ተስፋ ያደርጋሉ።