በቤንሻንጉል ጥቃት በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ሰዎች ቤተሰቦች ምን ይላሉ?
ምንጭ፡ BBC
አቶ ከሃሰ “እሳት ውስጥ የገባው ሰው ፀጋይ ነጋ ይባላል፤ ጓደኛዬ ነው። የአንድ ልጅ አባት ነበር፤ ወደ ልጁ እና ባለቤቱ እየተመለሰ ነው የተገደለው። ወደ ቦታው የሄዱ ሰዎች ፎቶ ላኩልን። በዚህ መንገድ ነው መገደሉን ያወቅነው” ይላል።
ከሃሰ የጓደኛውን መገደል የሚያሳይ ቪድዮ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከመሰራጨቱ በፊት ህይወቱ ማለፉን ለቤተሰቦቹ መነገሩን ይገልጻል። ከዚያ በኋላም ቪድዮውን ማየቱን ለቢቢሲ ተናግሯል።
በቤንሻንጉል ክልል መተከል ዞን በጉባ ወረዳ አይሲድ ቀበሌ ውስጥ የካቲት 24/2014 ዓ.ም የፀጥታ ኃይሎች ሲቪል ሰዎች ላይ ግድያ መፈፀማቸውን ኢሰማኮ ያወጣው ሪፖርት ያስረዳል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር የነበረው አሰቃቂ ቪዲዮ እንደሚያሳየው የፀጥታ ኃይሎቹ እና በርካታ ሰዎች በተሰበሰቡበት አስከሬኖች እና አንድ በሕይወት የነበረ ሰው በአሰቃቂ ሁኔታ በእሳት ሲቃጠሉ ያሳያል።
ኮሚሽኑ በማኅበራዊ ሚዲያ በስፋት የተሰራጨውን ይህንን ተንቀሳቃሽ ምስል በሚመለከት ምርመራ አድርጎ እንዳስታወቀው በአካባቢው የነበሩ የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር አውለዋቸው የነበሩ አስር ሰዎችን ከዳኝነት ውጪ ተኩሰው መግደላቸውን አመልክቷል።
እንደ ኢሰማኮ ሪፖርት ከሆነ ከተገደሉት አስር ሰዎች መካከል ስምንቱ በአካባቢው ነዋሪ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ በወቅቱ ድርጊቱን የተቃወሙ የጉሙዝ ተወላጆች ናቸው።
በሕይወት እያለ ወደ እሳት የተጨመረው ግለሰብ ማን ነው?
ቪድዮው ላይ በሕይወት እያለ እሳት ውስጥ የተጣለው ግለሰብ “ኧረ በእናታችሁ” እያለ ይማፀናል።
የልዩ ኃይል ደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች ደግሞ “አቃጥሉት፤ እኛም እንደዚህ ነው የተቃጠልነው” ሲሉ ይሰማል።
በዚህ ቪዲዮ ላይ ወታደራዊ የደንብ ልብስ የለበሱ እንዲሁም ሲቪል ሰዎች ተሰብስበው “እባካችሁ ተዉኝ” እያለ ሲማጸናቸው የነበረውን ግለሰብ እሳት ውስጥ ሲጨምሩት ይታያል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የመንግሥት የፀጥታ አካላት ከመተከል ዞን እስር ቤት የይለፍ ወረቀት ይዘው ወደ መኖሪያቸው ሲመለሱ የነበሩ ሰላማዊ ሰዎች ‘ከፍርድ ውጪ’ መገደላቸውን አሳውቋል።
የመንግሥት ቃል አቀባይ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው ይህን ድርጊት የፈጸሙ ሰዎች የሚመለከት የማጣራት ሥራ መጀመሩን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የተጎጂ ቤተሰቦች ምን ይላሉ?
አቶ ከሃሰ በእሳት ተቃጥሎ የሞተው ፀጋይ ነጋ ጓደኛው መሆኑን ገልጾ፣ በዳንጉር ከተማ ሰዳል ወረዳ በንግድ ሥራ ይተዳደር ነበር ይላል።
ከሐምሌ 21/2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ የካቲት መጨረሻ 2014 ዓ.ም ድረስ በመተከል ዞን ግልገል በለስ ማረሚያ ቤት ለሰባት ወራት ታስሮ መቆየቱንም ያስታውሳል።
የካቲት 23/2014 ዓ.ም ከሌሎች የትግራይ ተወላጆች ጋር ከእስር የተፈታው ፀጋይ ከማረሚያ ቤቱ ነጻ መሆኑን የሚገልጽ ወረቀት ተጽፎለት መያዙን ይናገራል።
“ወደ ቤተሰቦቹ በሚመለስበት ወቅት ልዩ ፍቃድ ስለሚያስፈልግ ወደ ቋንኩሮ እና ባምዛ ለሚገቡ የፈቃድ ወረቀት ተጽፎላቸው፣ በፀጥታ አካላት ታጅበው፣ በአንድ አውቶብስ ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ ነበሩ።”
ከሃሰ አክሎም አይሲድ በሚባል አካባቢ ሲደርሱ ጸጋይ እና ሌሎች አብረውት የነበሩ ሰዎችን ቻይና ካምፕ ወደ ሚገኝ ትምህርት ቤት ወስዷቸው ይላል።
በኋላም ሌሎቹ በጥይት ተመትተው ሲገደሉ፣ ጸጋይ በሕይወት እያለ መቃጠሉን ከሃሰ ያስረዳል።
በሪሁ ገብረሚካኤል አቶ ገብረመድኅን ከሚባል አጎቱ ጋር በእንስሳት እርባታ ሲተዳደር እንደነበር ይናገራል።
አቶ ገብረመድኅን ለ20 ዓመታት ያክል ጉባ ወረዳ ባምዛ ቀበሌ ላይ መኖራቸውን የሚገልጸው በሪሁ፣ ባለፈው ሐምሌ ወር በርካታ የትግራይ ተወላጆች በኮማንድ ፖስቱ ተይዘው ሲታሰሩ እርሱ ማምለጡን ገልጿል።
አጎቱ አቶ ገብረመድኅን “. . . ለሰባት ወራት ከታሰሩ በኋላ ባለፈው ሳምንት ተፈቱ። ከተፈቱ በኋላ ግን ወደ ሕዳሴ ግድብ በጥበቃ ነው የምትሄዱት ተብለው ነበር። ሆኖም በሕይወቱ እያለ በእሳት መቃጠሉ ተነገረኝ” ይላል።
በሪሁ ይህንን ይበል እንጂ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት ግን በሕይወት እያለ የተቃጠለው አንድ ሰው መሆኑን ያመለክታል።
መተከል ዞን ባምዛ ቀበሌ ተወልዶ ያደገው የአካባቢው ኗሪ አበበ ታረቀኝ በበኩሉ፣ ባለፈው የሐምሌ ወር ወላጆቹ በኮማንድ ፖስቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና በተንቀሳቃሽ ምስሉ ሁለት ወንድሞቹ በእሳት ሲቃጠሉ ማየቱን ለቢቢሲ ገልጿል።
“ሐምሌ 20 ላይ ስድስት የቤተሰብ አባላቶች በአንድ ላይ ታሰርን። እኔ ከሁለት ወር በኋላ ተፈታሁ። ታናሽ እና ታላቅ ወንድሞቼ፣ አባቴን ጨምሮ ግልገል በለስ ወደ ሚገኘው ማረሚያ ቤት ተወሰዱ። ሕዳር 30 ላይ ዳግም በመታሰሬ እና ወደ ግልገል በለስ ስለተወሰድኩ ማረሚያ ቤት ውስጥ አገኘኋቸው” ይላል።
ጥር 21 ላይ ከሁለቱ ወንድሞቹ በስተቀር ቀሪዎቹ የቤተሰቡ አባላት መፈታታቸው ያስታውሳል።
“ሁለቱንም ወንድሞቼን [ሮቤል ታረቀኝ [19] እና ገብረማርያም ገብረመድኅን (30)] ወደ ቤት ሲመለሱ ከመንገድ ስለመለስዋቸው ስልክ በመደወል ‘መልሰውናል፤ አንመጣም’ ብለው ነገሩን” ሲል ይናገራል።
አበበ ሁለቱም ወንድሞቹ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተሰራጨው ቪድዮ በሚታየው ሁኔታ በአሰቃቂ ሁኔታ መሞታቸውን ለቢቢሲ ገልጿል።
በሕዳሴ ግድብ ተቀጥሮ ይሰራ እንደነበር የሚናገረው ሐየሎም በበኩሉ ባለፈው ነሐሴ ወር ከሌሎች የትግራይ ተወላጅ የሥራ ባልደረቦቹ ጋር ጃዊ በሚባል በረሃ መታሰሩን ይገልጻል።
“የጁንታ ተባባሪዎች ናችሁ ብለው ጃዊ በረሃ ላይ አሰሩን። ከ30 በላይ ነበርን፤ በሁለት ከፍለው አሰሩን። እኔ ጋር የነበሩት በሙሉ ኢንጅነሮች ናቸው። በጣም መጥፎ አያያዝ ነው የነበረው . . .” ይላል።
ፍርድ ቤት በነጻ ሲያሰናብታቸው እርሱ ወደ ቤተሰቦቹ ሲመለስ አብሮት ታስሮ የነበረው ጓደኛው ግን ወደ ሥራ ቦታው በመሄድ ላይ እንደነበር ያስረዳል።
አክሎም “እኔ ለደኅንነቴ ስለሰጋሁ ሥራዬን ትቼ ወደ ቤተሰቦቼ መጣሁ። እርሱ ግን ወደ ግድቡ ሲሄዱ ከነበሩ ሰዎች ጋር አይሲድ ሲደርሱ ተገደለ። ከሳሊኒ ጋር ሲሰራ የነበረው ዘሚካኤል የሚባል ግለሰብም አይሲድ ላይ ተገደለ።”
በአጠቃላይ የካቲት 23 እና 28/2014 ዓ.ም ከማረሚያ ቤት የተፈቱ 30 የትግራይ ተወላጆች በመንግሥት የፀጥታ አካላት ተይዘው መገደላቸውን እነዚህ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቤተሰብ አባላት ያስረዳሉ።
ሆኖም ቢቢሲ እነዚህ ግድያዎች ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ሃሮን ዑመር በመተከል ዞን የመንግሥት የፀጥታ አካላት ፈጽመውታል የተባለው ግድያ እውነት መሆኑን አረጋግጠው “መተከል ወይ ግልገል በለስ በኮማንድ ፖስት ስለሚተዳደር ምርመራ እየተካሄደ ስለሆነ፣ ተጠርጠሪዎች ቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው። ስለሆነም ሙሉ ሪፖርት ሲደርሰን እንገልጻለን” የሚል መልስ ለቢቢሲ ሰጥተዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት የመተከል ዞን በመከላከያ ሠራዊት፣ በፌደራል ፖሊስ እንዲሁም ከልዩ ኃይል አባላት ተውጣጥቶ በተዋቀረ ኮማንድ ፖስት ስር ሲተዳደር ቆይቷል።
የጉዳዩ ምርመራ የሚገኝበት ደረጃ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቤንሻንጉል ክልል መተከል ዞን በጉባ ወረዳ አይሲድ ቀበሌ ውስጥ የካቲት 24/2014 ዓ.ም በመንግሥት የፀጥታ አባላት እና በሌሎች ተሳትፎ ጭምር ሲቪል ሰዎች ላይ ግድያ መፈፀሙን ገልጿል።
ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ላይ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከግልገል በለስ ከተማ ወደ ማንኩሽ እና ባምዛ ይጓዙ በነበሩ ሲቪል ሰዎች ላይ ፍተሻ ማካሄዳቸውን በሪፖርቱ ላይ አመልክቷል።
የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በአካባቢው ፍተሻ ማካሄድ የጀመሩት የካቲት 23/2014 ታጣቂዎች በከባድ መሳሪያ በመታገዝ በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ቁጥር ያላቸው የፀጥታ ኃይሎች እና ንፁሃን ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው።
የፀጥታ አባላቱ ባደረጉት ፍተሻም በቅርቡ ከእስር ተፈትተው ከመተከል ዞን ማረሚያ ቤት የይለፍ ወረቀት በመያዝ ወደ መኖሪያቸው የተመለሱና የአካባቢው ነዋሪዎች የነበሩ ስምንት ትግራይ ተወላጆችን በአካባቢው በተፈፀመው ጥቃት መወንጀላቸውን ሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል።
በወቅቱ በተደረገ ፍተሻ የወታደራዊ መገናኛ ሬዲዮ፣ ከ40ሺህ ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ እና የተለያዩ ፎቶግራፎች መያዛቸው ተገልጿል።
ከዚህ በኋላ የመንግሥት ፀጥታ አባላት ተጠርጣሪዎቹን እየደበደቡ ተጨማሪ መረጃ ሲጠይቁ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አንዱ “በአካባቢው በተፈጸመው ጥቃት ላይ እጃችን አለበት፤ ባምዛ በሚባለውና በግልገል በለስ ሰዎች አሉን” ማለቱን ተከትሎ፣ የመንግሥት የፀጥታ ኃይል አባላቱ ሁኔታውን የተቃወሙ ሁለት የጉሙዝ ተወላጆችን ጨምሮ 10 ሰዎችን ተኩሰው ገድለዋል ብሏል።
ቢቢሲ በኢሰማኮ የክልሎች ክትትል እና ምርምር ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ይበቃል ግዛውን በፀጥታ አካላት ታጅበው ከማረሚያ ቤት ወደ ቤታቸው የሚሄዱ ሰዎች እንዴት እና በምን አጋጣሚ እነዚህ እቃዎች እጃቸው ላይ ሊገኝ ቻለ? የሚል ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን እርሳቸውም መረጃውን አካባቢው ላይ ከነበሩ የዓይን እማኞች ማግኘታቸውን ገልፀዋል።
አክለውም የዓይን እማኞቹ የካቲት 23/2014 ዓ.ም በወታደር ታጅቦ እየሄደ በነበረው መኪና ላይ ስለደረሰው ጥቃት እማኝነታቸውን እንደሰጧቸውም ይናገራሉ።
“ከዚህ ውጪ ተጎጂዎቹ ከማረሚያ ቤት የወጡበት ሰአት፣ ተግባሩ ወደ ተፈጸመበት ቦታ እንዴት ደረሱ የሚለው ግን መረጃ የላቸውም። ከመተከል ዞን የይለፍ ወረቀት ይዘው ሲጓዙ የነበሩ እና ፍተሻ ሲደረግ የፀጥታ አካላት የመገናኛ ሬድዮ፣ ገንዘብ እና አልባሳት አግኝተናል ማለታቸው ነው የነገሩን” ይላሉ።
መንግሥት በዚህ ጉዳይ በሚያካሂደው ምርመራ እነዚህን ጉዳዮች ማጣራት እንዳለበትም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው “ችግሩን በፈጠረው ማንኛውም አካል ላይ መንግሥት እርምጃ ይወስዳል። የሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት እያጣሩ ነው፤ ይህም ሥራ ወዲያው ነው የተጀመረው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከኢሰመኮ ሪፖርት በኋላ የተፈፀመ ግድያ አለ?
በመተከል ዞን ተወልዶ ያደገው ሙሉጌታ የማነ፣ ወላጅ አባቱ አቶ የማነ ማሰ በአካባቢው ላለፉት 40 ዓመታት በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው ኑሯቸውን ይገፉ እንደነበር ይናገራል።
አባቱ እና ጓደኛቸው ለስምንት ወር ወደ አሶሳ ተወስደው መታሰራቸውን ሙሉጌታ ገልጿል።
የካቲት 28/2014 ዓ.ም አባቱ እና ጓደኛቸው ከአሶሳ ማረሚያ ቤት ተፈትተው ወደ ቤታቸው መመላሳቸው እና በማግስቱ በመንግሥት የፀጥታ አካላት መገደላቸውን ተናግሯል።
“አትምጣ ብንለውም፣ ሽማግሌ ነኝ፤ የት እሄዳለሁ ብሎ ወደ ቤቱ መጣ። ልጄ በሰላም ገብቻለሁ ብሎም ደወለልኝ። በነጋታው ግን ከምሽት 3፡00 ላይ የመንግሥት የጸጥታ አካላት መጥተው ወሰዱት። በ29 ገደሉት፤ . . .በአካባቢው የሚገኙ የጉሙዝ ብሄረሰብ ተወላጆች አስከሬኑን አንስተን እንቅበረው ቢሉም በአካባቢው ያሉት የፀጥታ አካላት አስከሬኑን እንዳያነሱ መከልከላቸውን ነገሩን” ይላል።
የቤንሻንጉል ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ሃሮን ዑመር በተለያዩ የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ታስረው የነበሩ የትግራይ ተወላጆች መፈታታቸው ገልፀዋል።
እነዚህ ሰዎች ከእስር ከተለቀቁ ለሁለት ሳምንት እንዳለፋቸው የሚገልፁት ኮሚሽነሩ፣ ግለሰቦቹ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ተመልሰዋል ይላሉ።
በፀጥታ አካላት ተገድለው አስከሬናቸው እንዳይነሳ ተከልክሏል ስለሚለው ክስ የተጠየቁት ኮሚሽነሩ፣ “በዝርዝር ስለ ማናውቀው ጉዳይ መናገር ያስቸግረናል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የመንግሥት ቃል አቀባዩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ መረጃ እንደሌላቸው በመግለጽ፣ የመንግሥት የፀጥታ አካላት ያለምክንያት ይህንን ድርጊት ሊፈጽሙ አይችሉም ሲሉ ተናግረዋል።