ገንዘባቸውን ገንዘብ በመክፈል የሚያገኙት የትግራይ ቤተሰቦች
ምንጭ፡ BBC አማርኛ
አዲስ አበባ የምትኖረው እና የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ትርሃስ ኃይሉ ትግራይ ላሉ ቤተሰቦቿ ገንዘብ ለመላክ ወደ ባንክ የሄደችበትን የመጨረሻ ቀን አትረሳውም።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የፌደራል መንግሥቱ መቀለን ለቅቆ ሲወጣ ትርሃስ በባንክ ቤት ለቤተሰቦቿ ገንዘብ እያስገባች ነበር።
“ከሥራ እንደወጣሁ በቀጥታ ወደ ባንክ ሄጄ እጄ ላይ የነበረውን አስገባሁ። ወደ ቤት ስመለስ የምሰማው ግን አስደነገጠኝ፤ አሁን ደግሞ ምን እየተፈጠረ ነው ብዬ ግራ ተጋባሁ። ከዚያ ቀን በኋላ ባንኮች በመዘጋታቸው ግን ቤተሰቦቼ ገንዘቡ አልደረሳቸውም” ትላለች።
ባለፈው ሰኔ ወር ላይ የትግራይ አማፂያን የመቀለ ከተማን እና አብዛኛውን የትግራይ አካባቢ ከተቆጣጠሩ በኋላ ትግራይ ላለፉት 11 ወራት ያህል የባንክ፣ የስልክና ሌሎች መሠረታዊ አግልግሎቶች እንደተቋረጡ ይገኛሉ።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በጀመረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ አገልግሎቶች ለተወሰኑ ወራቶች አገልግሎት መስጠት ጀምረው የነበሩ ቢሆንም፣ የፌደራል መንግሥቱ ከክልሉ ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ ዳግም ሙሉ በሙሉ ቆመዋል።
የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት መቀለን ለቅቆ በወጣበት ዕለት፣ ከከሰዓት በኋላ ጀምሮ የከተማዋ ነዋሪዎች ግራ በመጋባት ስሜት ውስጥ ሆነው ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላኛው የከተማዋ ጫፍ ሲሯሯጡ እንደነበር ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ያስታውሳሉ።
በዕለቱ ትጥቃቸውን የያዙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከተማዋን ለቅቀው ሲወጡ የንግድ ተቋማት፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ተቋማት ተዘግተው፣ በርካታ ሲቪል ሰዎች ወደ ቤታቸው አመሩ።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የባንክ፣ የስልክ እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች በትግራይ የውሃ ሽታ ሆነው ቀሩ።
ትርሃስ ዛሬም በትግራይ ለሚገኙ ቤተሰቦቿ ገንዘብ ትልካለች። ይህ ግን እንደ ከዚህ ቀደሙ በባንክ በኩል የሚከናወን አይደለም።
ለምታውቃቸው ደላሎች በመደወል የጠየቁትን የአገልግሎት ክፍያ በመክፈል የሚፈፀም መሆኑን ለቢቢሲ ታስረዳለች።
እኚህ ገንዘብ ተቀብለው ወደ ትግራይ የሚልኩ እና የሚያደርሱ ግለሰቦች ከ20 እስከ 40 በመቶ የሚደርስ ክፍያ [ኮሚሽን] እንደሚጠይቁ ቢቢሲ የተለያዩ ሰዎችን በማነጋገር መረዳት ችሏል።
እነዚህ ገንዘብ አዘዋዋሪዎች ለማድረስ የተስማሙትን ገንዘብ ወደ ባንክ ሂሳባቸው እንዲገባ የሚያደርጉ ሲሆን በስምምነታቸው መሰረትም የድርሻቸውን ቆርጠው ቀሪውን ያደርሳሉ።
እነዚህ ገንዘብ አዘዋዋሪዎች ከአዲስ አበባ ጀምሮ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች የሚገኙ መሆናቸውን ቢቢሲ መረዳት ችሏል።
በተጨማሪም በላኪ፣ ተቀባይ እንዲሁም በገንዘብ አዘዋዋሪ ደላላ መካከል ያለው ግንኙነት ‘በእምነት’ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ላኪዎች እና ደላሎች ይናገራሉ።
‘ . . . ብዙ የሚያለቅስ ሰው አለ’
የትግራይ ክልል ከአማራ ጋር በሚዋሰንበት አካባቢ የሚኖረው ኑረዲን (ስሙ የተለወጠ)፣ ይህንን ገንዘብ የማቀባበል ተግባር ከሚሰሩ በርካታ ደላሎች መካከል አንዱ ነው።
እርሱ እንደሚለው ገንዘቡን በትግራይ ለሚገኙ ቤተሰቦች ለማድረስ በርካታ ውጣ ውረዶችን ማለፍ ይጠይቃል።
በትግራይ ገጠር ቀበሌዎች የሚኖሩ ቤተሰቦች ገንዘብ ሲላክላቸው በእግር ረዥም ሰዓት በመጓዝ ማስረከብ ከሥራ ድርሻዎቹ መካከል አንዱ መሆኑን ለቢቢሲ ይናገራል።
ገንዘብ የሚልኩ ሰዎች፣ በሰው ወይም በስልክ እንደሚያገኙት የሚናገረው ኑረዲን፣ ይሄንን ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እራሱ ጭምር ወደ ተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች በመሄድ እና ክልሉ ውስጥ ከሚገኙ ተመሳሳይ ሥራ ከሚሰሩ ሰዎች ጋር በመተባበር ገንዘብ እንደሚያቀባብል ይናገራል።
“እኔ የሚልከውንም ሆነ የሚቀበለውን ሰው አላውቀውም፤ በመተማመን ብቻ ነው የምንሰራው። ወደ አላማጣ፣ መቀለ ወይም ውቅሮ ብቻ ሳይሆን ወደ ገጠሮች ጭምር እስከ ስምንት ሰዓት በእግር ተጉዤ ገንዘብ ያደረስኩላቸው ቤተሰቦች አሉ። የእነርሱን ሁኔታ ሳይ የሰው ህይወት እያዳንን እንዳለን ይሰማኛል” ይላል።
አንድ በትግራይ ውስጥ ለሚገኙ ቤተሰቦቹ ገንዘብ መላክ የሚፈልግ ሰው ከአዲስ አበባ እስከ አፋር፣ አማራ እና መቀለ ያሉ ደላሎች ጋር ስልክ በመደወል፣ ገንዘቡን የሚቀበሉ ሰዎች የሚኖሩበት ወይ ይገኙበታል ተብሎ የሚታሰበው ቦታ መረጃ መስጠት ይጠበቅበታል።
“የቤት ወይም የብሎክ ቁጥር ሊሆን ይችላል የሚነገረን። እኛ ደግሞ የተቀባዩ ስም እና መታወቂያ አይተን እንሰጣቸዋለን። አገልግሎት እየሰጠን ነው ብዬ ነው የማምነው፤ ሲቀበሉን ለላኪው ገንዘቡን መድረሱን ለማረጋገጥ አጭር ቪድዮ ቀርጸን እንልክለታለን፤ በዚያው ሰላምታ ይደርሰዋል” ሲል ኑረዲን ያስረዳል።
በዚህ የገንዘብ ማስተላለፍ ሥራ ውስጥ ብቻውን እንዳልሆነ የሚናገረው ኑረዲን የሚላከውን ገንዘብ ለማድረስ 30 እና 40 በመቶ ኮሚሽን እያስከፈሉ ተመሳሳይ ሥራ የሚሰሩ ግለሰቦች ቢኖሩም፣ እርሱ ግን ለአገልግሎቱ 20 በመቶ ብቻ እንደሚቀበል ገልጿል።
ኑረዲን የአገልግሎት ክፍያውን ከፍ ያለበትን ምክንያት ሲያብራራ ገንዘቡ ከባንክ ወጥቶ ተጠቃሚዎቹ እጅ እስኪደርስ ድረስ ያለው ሰንሰለት እጅግ ረጅም፣ የተሳሰረ፣ አደገኛ እና ብዙ የትርፍ ተካፋዮች ያሉት በመሆኑ ነው ይላል።
“የምንወስደው ኮሚሽን በአጠቃላይ ኪሳችን ውስጥ አይገባም። አንድ ጊዜ ገንዘብ ከባንክ ስናወጣ ለብዙ ሰዎች የሚሆን ነው የምናወጣው። ከባንክ በአንድ ጊዜ ከፍተኛ ገንዘብ ማውጣት ስለማይፈቀድ የሻይ የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። በተጨማሪ ትግራይ ውስጥ ብዙ ገንዘብ ይዞ መንቀሳቀስ አይፈቀድም። እንደዚህ አይነት መሰናክሎችን በገንዘብ ነው የምንሸፍናቸው።”
አያይዞም “ከ10 ሺህ ብር 500 ቢደርሰን ነው፤ ቀሪው መንገድ ላይ ለሚገጥሙን ችግሮች መሸፈኛ ይውላል። እንደዚያም ሆኖ የአንድ ሰው ህይወት እንታደጋለን። የሚገርመው እዚያ [ትግራይ] ሰው እያለቀሰ ነው፤ ገንዘብ እያለው እየተራበ ነው” በማለት ኑረዲን ሁኔታውን ያስረዳል።
የዚህ ገንዘብ ዝውውር ሰንሰለት እጅግ አደገኛ እና መንግሥት እና የፀጥታ አካላት ቁጥጥር የሚያደርጉበት ስለሆነ በዚህ መንገድ የተገኘ ገንዘብ ሊወረስ፣ ሕገወጥ ሥራው ላይ ሲሳተፉ የተገኙ ሰዎች ደግሞ ሊታሰሩ ይችላሉ።
ባለፈው ሳምንት የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን፣ በድብቅ ወደ ትግራይ ሊገባ ነበረ የተባለ በሰሜን ወሎ ቆቦ ከተማ በኩል 3 ሚሊዮን ብር፣ በሰቆጣ ከተማ ደግሞ 5 ሚሊዮን ብር እና 20 ተጠርጣሪዎች በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዘግበዋል።
እነዚህን መረጃዎች መስማቱን የሚጠቅሰው ኑረዲን “ገንዘቡ ለህወሓት ነው ቢባልም እኛ ግን ገንዘቡን ለግለሰቦች ነው የምናደርሰው። ይሄንን ሥራ ስንሰራ ገንዘቡ ሊወረስ እኛም ልንታሰር እንደምንችል ይገባናል። የተራቡ ሰዎች ደግሞ አሉ፤ ብዙ ቤተሰቦች ገንዘቡ ትንሽ ቢሆንም ስናደርስላቸው ወላሂ እያለቀሱ ነው የሚያመሰግኑን። ይህ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው” ይላል።
ብቸኛው አማራጭ
ባለፉት ሳምንታት የህወሓት ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የዞን እና የከተማ አስተዳዳሪዎች የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሲያነጋገሩ ነበር።
በእነዚህ መድረኮች ላይ ነዋሪዎች በርካታ ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን፣ ከልጆቻቸው የሚላክላቸውን ገንዘብ ለመቀበል እየተከፈለ ስላለው የገንዘብ መጠን ‘እንደሚያነገብግባቸው’ ተናግረው ነበር።
አንድ የመቀለ ከተማ ነዋሪ ‘ወላጆች ያሳልፉልናል ብለው ቤት ንብረታቸውን አስይዘው የላኩዋቸው ልጆች፣ ወላጆቻችን ተዘግተዋል ብለው በሰው አገር ሰርተው ያገኙት ገንዘብ ይልካሉ። ሆኖም በአላማጣ 30 በመቶ እየተከፈለበት ነው፤ አሁን ደግሞ አርባ አድርሰውታል። ይሄንን አልፈውም የእኩል መካፈል ደርሰዋል። ሰው ታዲያ ምን ሊበላ ነው? ኧረ ሕግ ይውጣበት!’ ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው “40/60 የሚባል ተጀምሯል። 10 ሺ ብር ተልኮልን ስድስት ሺ ብቻ ነው የምንቀበለው። ነጋዴዎች ለምንድን ነው የሚፈሩት? ቴሌቪዥን ላይ የተራበ ልጇን የያዘች እናት እያዩ የማያማቸው ከሆነ ለምንድን ነው መንግሥት የማያየው?” ሲሉ ጠይቀዋል።
በመሆኑም መንግሥት በከተማ ላይ በዚህ ሥራ ተሰማርተው በሚገኙት ግለሰቦች ላይ እርምጃ እንዲወስድ፣ ከበባውን እንዲነሳ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ማግኘት የሚቻልባቸው ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ነዋሪዎች ሲጠይቁ ታይተዋል።
ቤተሰቦች የሚላክላቸውን ገንዘብ እስከ 40 በመቶ ከፍለው ለመቀበል መገደዳቸው ቢያማቸውም፣ ገንዘቡን የሚልኩ የቤተሰብ አባላት በበኩላቸው “ችግር ላይ ላሉ ቤተሰቦቻችን መድረስ የምንችልበት ብቸኛ አማራጭ ነው” ይላሉ።
እኔ ገንዘብ የምልከው በአፋር በኩል ነው የሚለው ሰመረ ገብረማርያም፣ በቅርቡ 25 በመቶ ከፍሎ ወደ ቤተሰቦቹ ገንዘብ መላኩን ይናገራል።
“የምንከፍለው በዛም አነሰም አራጣ በሚመሰል መልኩ ብዙ ገንዘብ እየከፈልን ነው። ግን ሌሎች አማራጮች ዝግ ናቸው፤ ባንክ የለም። ስለዚህ ቤተሰብ ገንዘብ በማጣት ከሚራብ 40 በመቶም ቢሆን ከፍለን መላክ ይሻላል፣ አማራጭ የማጣት ውሳኔ ነው” ብሏል።
ትግራይ ከሌላው የአገሪቱ ክፍል ተቆራርጣ ከቀረች ጊዜ አንስቶ በክልሉ የተፈጠሩ ችግሮች ከባድ መሆናቸው እንዲሁም ሕዝቡም ቅሬታውን በተለያየ መንገድ እየገለፀ መሆኑን የሚናገረው ደግሞ ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ የፖሊስ ባልደረባ ነው።
ይህ ግለሰብ ወደ ትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች ገንዘብ እየተላከበት ያለው ሰንሰለት ከአዲስ አበባ ጀምሮ ወልዲያ፣ አፋር እና ትግራይ የሚገኙ ሰዎች የተሳሰሩበት እንደሆነ ገልጿል።
“ካለኝ ተሞክሮ” ይላል ይህ የፖሊስ ባልደረባ “እንዲህ ያለ የተደራጀ “የወንጀል ቡድን” ሕጋዊ ካልሆነ ኢኮኖሚ ወይም ቢዝነስ፣ ሕጋዊ ያልሆነ ትርፍ እና የገንዘብ ጥቅም ማግኘትን አላማ አድርጎ የሚንቀሳቀስ ነው።”
እንዲህ አይነቱ ሁኔታ ደግሞ መንግሥት የማይሰራው ነገር ሲኖር ወይም በአስተዳደር አቅም ማነስ ምክንያት አቅርቦት ሲጓደል የሚፈጠሩ ናቸው ሲል ያብራራል።
“ለምሳሌ ወደ አንድ ቦታ አቅርቦት መድረስ ካልቻለ ኮንትሮባንዲስቶች ይገባሉ፤ መንግሥትን ተክተው ደግሞ ሥራቸውን እየሰሩ ትርፋቸውን ይወስዳሉ። እንደዚህ አይነት ችግር [ጦርነት] ሲፈጠር ደግሞ አጋጣሚውን የሚጠቀሙ ሰዎች ይፈጠራሉ። አሁን በትግራይ ሁሉም ነገር በመዘጋቱ ማንኛውም ነገር ለወንጀለኛ ሰጥቶ ማሰራት የተለመደ ይሆናል” ሲል ያብራራል።
በአሁኑ ወቅት በትግራይ የገንዘብ እና ሌሎች መሠረታዊ አቅርቦቶች እጥረት መኖሩን፣ ፍላጎቱ ደግሞ ከፍተኛ በመሆኑ መደበኛ ባልሆነ መንገድ የንግድ እና ሌሎች ሥራዎችን የሚሰሩ ነጋዴዎች እና ግለሰቦች እንዲበራከቱ ምክንያት መሆኑን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግለሰቦች ያስረዳሉ።
ሆኖም የትግራይ አመራር ከክልሉ ውጪ ያሉ እንቅስቃሴዎች የመቆጣጠር መብት እንደሌለው ይህ የፖሊስ ባልደረባ ይናገራል።
“ክልሉ ውስጥ ያለውንም ቢሆን ለመቆጣጠር አቅም የለውም። ያበረታታሉ ባልልም ይህንን መንገድ ሕዝብ እየጠቀመ ስለሆነ ማቆም አይችሉም። ከዚህ ባለፈ ግን ሙስናም ሊኖር ይችላል” ብሏል።